ስላት የተወ (የማይሰግድ)ሰው ፍርድ
ምድቦች
ምንጮች
Full Description
ሰላት የተወ (የማይሰግድ) ሰው ፍርድ
ዝግጅት ፦ ሼኽ ሙሐመድ ቢን ሳሊህ አልዑሰይሚን
ትርጉም ፦ መሐመድ ሐሰን ማሜ
ምስጋና ለአላህ ይገባው ፤ የአላህ ሰላትና ሰላም በመልእክተኛችን ሙሐመድ፤ በቤተሰባቸውና በባልደረቦቻቸው ላይ ይስፈን ::
ውድ ሙስሊም ወንድሜ ሆይ ! ይህ ለሼኽ ሙሐመድ ቢን ሳሊህ አልዑሰይሚን (አላህ ይዘንላቸውና ) የቀረበ ጥያቄና የሰጡት ምላሽ ነው ::
ጥያቄ ፦ አንድ ሰው ቤተሰቦቹን ሰላት እንዲሰግዱ ቢያዛቸውና ባይሰሙት : ከነርሱ ጋር አብሮ መኖር ነው ያለበት ወይንስ ቤቱን ለቆ መውጣት ?
መልስ ፦ እነዚህ ቤተሰቦች በጭራሽ የማይሰግዱ ከሆኑ ከሃዲያንና ከኢስላም የወጡ ናቸው ማለት ነው :: ስለሆነም ከእነሱ ጋር አብሮ መኖር አይችልም :: ነገር ግን ለነርሱ በተደጋጋሚ ጥሪ ሊያደርግላቸው ይገባል በርሱ ላይም ግዴታ ነው :: ምክንያቱም በቁርኣን ፤ በሀዲስ፤ በሰሃቦች ንግግርና በትክክለኛው ሚዛን መሰረት ሰላት የተወ (የማይሰግድ)ሰው አላህ ይጠብቀንና ካፊር ነውና ::
ቁርኣናዊ ማስረጃ
አላህ ሙሽሪኮችን(በአላህ ላይ የሚያጋሩትን) በማስመልከት እንዲህ ብሏል :
" فَإِن تَابُوا وَأَقَامُوا الصَّلوة وَءَاتَوُا الزَّكَوةَ فَإِخْوَانُكُمْ في الدِّينِ " التوبة 11.
" ከተፀፀቱ ፤ሰላትንም ከሰግዱ ዘካንም ከሰጡ የሃይማኖት ወንድሞቻችሁ ናቸው " አት_ተውባህ_11
አንቀጹ የሚያስገነዝበው ቁም ነገር እነዚህን ተግባራት ካልፈፀሙ ወንድሞቻችን እንደማይሆኑ ነው :: እስላማዊ ወንድማማችነት ከኢስላም በሚያስወጣ የክህደት ተግባር ቢሆን እንጂ በማንኛውም ትልቅ ወንጀል ቢሆንም እንኳ በቀላሉ አይፈርስም ::
ሃዲሳዊ ማስረጃ
የአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም)እንዲህ ብለዋል :
" بَيْنَ الرَّجُلِ وَبَيْنَ الكُفْرِ وَالشِّرْكِ تَرْكُ الصَّلاَةِ " رواه مسلم .
" በሰውየውና በክህደት እንዲሁም በማጋራት መካከል ያለው ልዩነት ሰላት ነው" (ሙስሊም ዘግበውታል): ቡረይዳህ (ረድየ ላሁ ዐንሁ)ባስተላለፈው ሀዲስ ላይም እንዲህ ብለዋል :-
" العَهْدُ الذِّي بَيْنَنَا وَبَيْنَهُمْ الصَّلاَةُ ، فَمَنْ تَرَكَهَا فَقَدْ كَفَرَ " رواه الترمذي ، وقال : حديثٌ حَسَنٌ صَحِيحٌ.
:" በእኛ እና በእነርሱ(በከሃዲያን)መካከል ያለው መለያ (ቃል ኪዳን) ሰላት ነው ፤ (ሰላትን)የተወ በእርግጥም ክዷል " (አት_ቲርሙዚ ዘግቦታል)
የሰሃቦች ንግግር
ይህን አስመልክቶ ከሰሃቦች አንደበት የተነገሩ መልእክቶች በርካታ ናቸው :
_ ዑመር (ረድየ አላሁ ዐንሁ) እንዲህ ብሏል፦
" لاَ حَظَّ فِي الإِسْلاَمِ لِمَنْ تِرَكَ الصَّلاَةَ " .
: " ሰላት የተወ ሰው በኢስላም ውስጥ ምንም እድል (ድርሻ ) የለውም:: " እድል(ድርሻ ) የሚለው ቃል ጥቅል ቃል ነው :: ስለሆነም አነሰም በዛም በኢስላም ውስጥ ምንም አይነት ቦታ እንደሌለው ያስረዳል::
_ ዐብዱላህ ኢብኑ ሸቂቅም( ረድየ አላሁ ዐንሁ )እንዲህ ይል ነበር፦
" كَانَ أَصْحَابُ النَّبِيِّ ﷺ لاَ يَرَوْنَ شَيْئًا مِنَ الأَعْمَالِ تَرْكُهُ كُفْرٌ غَيْرُ الصَّلاَةِ "
“ የአላህ መልእክተኛ ባልደረቦች ቢተው (ቢቀር) ክህደት ነው ብለው ከሰላት ውጭ የሚቆጥሩት ነገር አልነበረም "
ከትክክለኛው አእምሯዊ ሚዛን አንፃር
ከትክክለኛ አእምሯዊ ሚዛን አንፃርም ስንመለከተው ማንኛውም በልቡ ውስጥ ቅንጣት ያክል ኢማን ያለው ሰው የሰላትን ደረጃና አላህ የሰጠውን ቦታ እያወቀ ሰላትን እርግፍ አድርጎ ይተዋል ተብሎ ይታሰባልን?!በፍፁም
_ ሰላት የተወ (የማይሰግድ)ካፊር አይባልም ( ከኢስላም አይወጣም) ያሉት እንደ ማስረጃነት ያጣቀሷቸውን ሳስተውል ከአራት ሁኔታዎች እንዳማይወጣ ሆኖ ነው ያገኘሁት፦
1_ በመሰረቱ ለተባለው ጉዳይ አስረጅ አይደለም
2_ ሰላትን መተው እንደማይገባ በሚያመላክት ባህሪ(ገለፃ)የተገደበ ይሆናል
3_ አንዷን ሰላት በመተው ዑዝር ()በመስጠት ላይ የተገደቡ ናቸው
4_ ሰፊ መልእክት ያላቸው ይሆኑና ክህደት( ኩፍር)መሆኑን በሚያረጋግጡ አንቀፆች የተገደበና የተብራራ ይሆናል
ሰላት የማይሰግድ ካፊር(ከሃዲ) እንደሆነ ግልፅ ከሆነ ፤ ከኢስላም የወጡ ሰዎች ህግጋት ይመለከተዋል ማለት ነው።
(ሰላት የማይሰግድ ሙእሚን ነው፤ ጀነት ይገባል፤ከእሳት(ከቅጣት) ነፃ ይወጣል እና የመሳሰሉትን የሚያመለክት ማስረጃ የለም። በመሆኑም ሰላት የማይሰግድ " ከሀዲ ነው " የሚለውን “ፀጋን መካድ" ማለት ነው አልያም “መለስተኛ ክህደት ነው" ወደሚለው ግንዛቤ እንድንጓዝ አያደርገንም ።)
እንዲህ ከሆነ የሚከተሉት ህግጋቶች ይመለከቱታል ፦
አንደኛ፡ አይዳርም(እርሱን ማጋባት አይቻልም ) ፡የማይሰግድ ሆኖ የጋብቻ ውል ቢፈፀም ጋብቻው ትክክል አይሆንም ፡በዚህ ውልም ባለቤቱ አትፈቀድለትም ምክኒያቱም አላህ (I)የተሰደዱ ሴቶችን አስመልክቶ እንዲህ ብሏልና፦
“ فَإِنْ عَلِمْتُمُوهُنَّ مُؤْمِنَاتٍ فَلاَ تَرْجِعُوهُنَّ إِلَى الكُفَارِ لاَ هُنَّ حِلٌّ لَهُمْ وَلاَ هُمْ يَحِلُّونَ لَهُنَّ " الممتحنة – 10.
" አማኝ መሆናቸውን ካወቃችሁ ወደ ከሃዲያን አትመልሷቸው (ምክኒያቱም) እነርሱ (ሴቶቹ)ለእነርሱ(ለወንዶቹ) የተፈቀዱ አይደሉምና፡እነርሱም (ወንዶቹ) ለእነርሱ አይፈቀዱምና " አልሙምተሒና 10
ሁለተኛ፡ የጋብቻ ውል ከተፈፀመ በኋላ ሰላት ቢያቆም (ቢያቋርጥ)ጋብቻው ይፈርሳል፤ ባለቤቱም ለእርሱ የተፈቀደች አትሆንም ። ለዚህም ማስረጃ ያለፈው አንቀፅ ነው ።
ሦስተኛ፡ ይህ ሰው ቢያርድ እርዱ አይበላም ። ለምን ? ከተባለ ? ክልክል ስለሆነ ነው መልሳችን ። በአንፃሩ ደግሞ አንድ አይሁዳዊ ወይም ክርስቲያን ያረደውን መብላት ይፈቀድልናል ። በዚህም የተነሳ የዚህ ሰውዬ እርድ _አላህ ይጠብቀንና _ ከአይሁድና ከክርስቲያን እርድ የከፋ ይሆናል ማለት ነው ።
አራተኛ፡ መካ ወይም የመካን ክልል አልፎ መግባት አይፈቀድለትም ። ምክኒያቱም አላህ(I)እንዲህ ብሏልና፦
" يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا إِنَّمَا المُشْرِكُونَ نَجَسٌ فَلاَ يَقْرَبُوا المَسْجِدَ الحَرَامَ بَعْدَ عَامِهِمْ هَذَا " التوبة 28.
" እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አጋሪዎች እርኩሶች ናቸው። ከዚህም ዓመታቸው በኋላ የተከበረውን መስጊድ አይቅረቡ። " አት_ተውባህ፡28
አምስተኛ፡ ከዘመዶቹ አንዱ ቢሞት ውርስ የመካፈል መብት የለውም። ለምሳሌ ፦ አንድ ወላጅ ሰላት የማይሰግድ ልጅ (ወላጅ ሙስሊም ሆኖ ሰጋጅ ነው ልጁ ግን ሰጋጅ አይደለም) እና ራቅ ያለ የአጎት ልጅ ጥሎ ቢሞት ማነው ሊወርሰው የሚገባው ? ከተባለ
መልሱ: ወራሽ የሚሆነው የገዛ ልጁ ሳይሆን የአጎቱ ልጅ ነው ። ምክንያቱም የአላህ መልእክተኛ ኡሣማህ ባስተላለፈው ሀዲስ ላይ እንዲህ ብለዋል ፦
" لاَ يَرِثُ المُسْلِمُ الكَافِرَ وَلاَ الكَافِرُ المُسْلِمَ" متفق عليه .
" ሙስሊም የሆነ ከሃዲን አይወርስም ፤ ከሃዲ የሆነም ሙስሊምን አይወርስም። " (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)እንዲህም ብለዋል ፦
" أَلْحِقُوا الفَرَائِضَ بِأَهْلِهَا ، فَمَا بَقِيَ فَلِأَوْلَى رَجُلٍ ذَكَرٍ " متفق عليه .
“ ውርስን ለሚገባው አድርሱ የተረፈውን ቅርብ ለሆነ ወንድ ወገን ስጡ " ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል ።
ይህ እንደ ምሳሌ የተጠቀሰ ሲሆን ወራሾችን ሁሉ የሚመለከት ነው።
ስድስተኛ፡ ቢሞት ሬሳው አይታጠብም ፤ አይገነዝም ፤ አይሰገድበትም፤ ከሙስሊሞችም ጋር አይቀበርም ። ምን ይደረግ ከተባለ ፡ ጭር ያለ ስፍራ ይወሰድና ጉድጓድ ተቆፍሮ ከነልብሱ እንቀብረዋለን ። ምክንያቱም ለየት ያለ ክብር የለውምና። በዚህም መሰረት ማንኛውም ሰው የማይሰግድ ዘመድ ከሞተበት መስጅድ አምጥቶ ማሰገድ አይፈቀድለትም ።
ሰባተኛ፡ የቂያማ ቀን ከክህደት መሪዎች ማለትም ከፊርዐውን፡ከሃማን፤ ከቃሩንና ከኡበይ ኢብኑኸለፍ ጋር አብሮ ይቀሰቀሳል ። ጀነትም አይገባም ፡ ቤተሰቡም ማንም ቢሆን እዝነትንና ምህረትን ሊማፀኑለት አይገባም ። ምክንያቱም ከሃዲ ነው ፤ እንዲሁም አላህ እንዲህ ብሏል ፦
" مَا كَانَ لِلنَّبِيِّ وَالذِّينَ آمَنُوا أَن يَسْتَغْفِرُوا لِلْمُشْرِكِينَ وَلَوْ كَانُوا أُولِي قُرْبَى مِن بَعْدِ مَا تَبَيَّنَ لَهُمْ أَنَّهُمْ أَصْحَابُ الجَحِيمِ " التوبة 113.
“ ለመልእክተኛውም ይሁን ለማንኛውም አማኝ የእሳት ጓድ መሆናቸው ግልፅ ከሆነላቸው በኋላ የቅርብ ዘመድ ቢሆኑም እንኳ ለሙሽሪኮች ምህረትን ሊጠይቁላቸው አይገባም ።“ ( አት_ተውባህ 113)᎐
ውድ ወንድሞቼ ጉዳዩ እጅግ አንገብጋቢና አደገኛ ነው። ከመሆኑም ጋር በጣም የሚያሳዝነው አንዳንድ ሰዎች ይህን ጉዳይ ችላ በማለት የማይሰግድ ሰው እቤታቸው ያስቀምጣሉ ነገሩ ክልክል ሆኖ ሳለ ።
ሰላት የተወ ሰው ወንድም ሆነ ሴት ፍርዱ ይህን ይመስላል
ሰላትን የተውክና የዘነጋሃት ሆይ ! የቀረውን እድሜህን መልካም ሥራ በመስራት ተጠቀምበት ፡ ከእድሜህ ምን ያክል እንደቀረህ አታውቅምና ወራት ፤ ቀናት ፤ ሰዓታት ?
የዚህ ሁሉ እውቀት አላህ ዘንድ ብቻ ነው።
ቀጥሎ ያለውን የአላህ ቃልን ዘውትር አስታውስ ፡
" إِنَّهُ مَن يَأْتِ رَبَّهُ مُجْرِمًا فَإِنَّ لَهُ جَهَنَّمَ لاَ يَمُوتُ فِيهَا وَلاَ يََحْيَ " طه - 74
" እነሆ ከሃዲ ሆኖ ወደ ጌታው የሚመጣ ሰው ለእርሱ ገሀነም አለችለት ፤ በውስጧም አይሞትም ህያውም አይሆን "ጣሃ 74
እንዲህ የሚለውንም ቃል አስታውስ ፡
{فَأَمَّا مَنْ طَغَى (37) وَآثَرَ الْحَيَاةَ الدُّنْيَا (38) فَإِنَّ الْجَحِيمَ هِيَ الْمَأْوَى (39)} [النازعات: 37 - 39]
" የካደ ሰውማ ፤ ቅርቢቱንም ህይወት የመረጠ ፤ ገሀነም እርሷ በእርግጥ መኖሪያው ናት " አልናዚዓት ፡ከ 37_39
አላህ ለመልካም ነገርና ለጥሩ እድል እንዲያበቃህ ፤ እንዲሁም የተቀረውን እለትህን በእውቀት፤ በስራና በዳዕዋ በሸሪዓ ጥላ ስር የምታሳልፍ ያድርግልህ ስል እማፀነዋለሁ
ወሰለላሁ ዓላ ነቢዪና ሙሀመዲን ወዓላ ኣሊሂ ወሰሕቢሂ ወሰለም